-በዘውገ አባተ (ኦ.ዩ.)
እንደመግቢያ
በ411 ገጾች (አባሪ ሳይጨምር) የቀረበው “ጥሎ ማለፍ“ ታሪካዊ ልቦለድ ከደርግ የ17 ዓመታት የአገዛዝ ዘመናት የመጀመሪያዎቹን ወሳኝ 14 ዓመታትና በአመዛኙ አዲስ አበባን መቼቱ በማድረግ መጠላለፍ የበዛበትን የዘመኑን የፖለቲካ ሕይወት የሚተርክ ነው። ደራሲው በመግቢያው እንደገለጸው ታሪካዊ ልቦለዱ “ካንድ የደርግ ቋሚ ኮሚቴ አባል ከነበረ ግለሰብ ሕይወት ዙሪያ የተጠነጠነ ነው።“ (ገጽ 6) ከዚህ አልፎ ግን የታሪካዊ ልቦለዱ ማዕከል የሆነው ዳኛቸው ወረደ የዘመኑን ፖለቲካዊ ገጽታና ድባብ፥ የባለሥልጣናቱን ሥነ ልቡናዊ፥ አእምሯዊና ፖለቲካዊ ማንነት ይናገርበት ዘንድ ደራሲው ከምናቡ አንቅቶ የተጠቀመው ገጸ ባሕሪ ይሁን አለያም አንድ በሕይወት የነበረን የደርግ አባል ሰብእና በመውሰድ ታሪኩን የጥበብ ሥጋ አልብሶ፥ የጥበብ እስትንፋስ ይዝራበት (እውነቱ ይኸኛው ይመስላል) ተብራርቶ የተነገረን ነገር የለም። ነገር ግን ከላይ በጠቀስኳቸው በሁለቱም መንገድ ይሁን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሙሉ በሙሉ የፈጠራ ውጤት በሆነ ገጸ ባህሪ በኩል ታሪካዊ ልቦለድን ማቀበል ይቻላል። ቁምነገሩ በሚነገረን ታሪክና ታሪኩ በሚወክለው ጊዜና ቦታ (መቼት) መካከል ባለው እውነተኛ ተዛምዶ ላይ ይመስለኛል።
መጽሃፉን እንዲያው በወፍ በረር ከሦስት የልቦለድ ዓላባውያን አኳያ ለመመልከት እሞክራለሁ። ‘‘ጥሎ ማለፍ‘‘ በቅርጽም ዳጎስ በይዘትም ሰፋ ብሎ የቀረበ ስራ እንደመሆኑ፣ መጽሃፉን በምልዓት ወይም በጥልቀት ለመቃኘት ጊዜውም አልነበረኝም። ድፍረቱንም አልሞክረውም። የመረጥኳቸው የመመልከቻ መነጽሮች የገጸ ባህሪ አሳሳል (ከዋናው ገጸ ባሕሪ አንጻር)፣ ታሪኩና ቋንቋው ናቸው። ከላይ በጠቀስኩት ቅደም ተከተል መሠረት እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ።
ሀ. ዋናው ገጸ-ባህሪ
የታሪካዊ ልቦለዱ ማዕከል እንደመሆኑ መጠን ዋናውን ገጸ-ባህሪ ዳኛቸው ወረደን የምንተዋወቀው ወዲያውኑ ታሪኩ ሲጀምር ነው። በገጸ ባህሪው ገለጻ በሚጀምረው ታሪክ የዳኛቸው ዕድሜ፥ ፖለቲካዊ አቋምና ፍላጎት፥ ወታደራዊ ማእረግና ቤተሰባዊ ዳራ ጥርት ባለና ባልተንዛዛ አቀራረብ ተነግሮናል። በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ገጾች ንባባችን ሰውዬው የዋዛ ባለሥልጣን እንዳልነበር፥ በአብዮቱ የለውጥ ሂደት ጉልህ ሚና እንደተጫወተ፥ በኋላም በደርግ አስተዳደር ኮሚቴ አባልነቱ ላይ ያፈ ደርግነት ሥልጣንም የተመረቀለት ሰው መሆኑን ስለምናውቅ መጽሃፉ ካንድ ቁልፍ የደርግ ሰው ታሪክነት ባሻገር በዚህ ሰው በኩል ዘመኑንና የዘመኑን የከባድ ሻምፒዮና ተጠላላፊዎች (Heavy weights) ማህበረ ፖለቲካዊ ጣጣ ፈንጣጣ እንዲያም ሲል የጊዜውን ወሳኝ ታሪካዊ ክስተቶች የምናይበት ድርሳን እንደሚሆን እንገነዘባለን።
ዳኛቸው ወረደ ዘመኑን ራሱን ሆኖ የሚቀርብባቸው አብነቶች ጥቂት አይደሉም። እንደማስታወቂያ ሹምነቱ የሳንሱር መቀስ ነው። ባንድ ቀን ከቀረቡለት አሥራ ሁለት አገር አቀፍ ዜናዎች ውስጥ ሰባቱን ሲሰርዝም ሆነ ሌሎቹን ሲያሳልፍ ምክንያቱ ሙያዊ ሳይሆን፣ ጭፍን የደርግ ወገናዊነት ነው። ርምጃው የቀረበበት ዝርዝርና የስረዛው ሂደት የደርግን ጨካኝ ሳንሱር በመወከል የቆመ ይመስላል። በመጽሃፉ እንደተጠቀሰውም እንደ ያብዮት ዜና ማእከል ኃላፊነትቱ “በዳኛቸው ጠረጴዛ ስር የማያልፉ ጉዳዮችና ምስጢሮች አልነበሩም። (ገጽ 16) የስልጣኑ ወሳኝነትም “ዋነኛ የደርግ መረጃዎች ማእከል ሆኖ ነበር - ዳኛቸው እራሱ“ (ገጽ 17) በሚል ተቋም አከል ውክልና የተገለጸ ነው።
በደርጉ ላይ ያለው እምነት እንደተልባ ሥፍር ይንሸራተት በነበረው የሕዝቡ እምነት (ሕዝቡ በደርግ ላይ የነበረው እምነት ለማለት ነው) መሃል ቀጥ ብሎ የቆመ መሆኑ በአንድ በኩል ለቆመለት ዓላማ ያለውን ቁርጠኝነት፥ በሌላ በኩል እምነቱና ድርጊቶቹ ከሕዝቡ እምነትና ፍላጎት የተፋቱ መሆኑን ያመለክታል። እርግጥ ነው የሕዝቡ በሥርዓቱ ላይ እምነት ማጣት ያሳስበዋል። ሆኖም ሥርዓቱ “ነህ“ የተባለውን አለመሆኑን በተግባር በማረጋገጥ የሕዝብን ጥርጣሬ መሻር እንደሚገባው አይታየውም። ለምሳሌ “የደርግ ወታደራዊ መንግሥት የቆመለት መደብ የንኡስ ከበርቴው ነው። የገበሬው መደብ ትግል በተዳከመ ቁጥር ደርግ የብዙሃኑ ጠላት ይሆናል“ የሚለው የዘመኑ ትችት ቢያሳስበውም ለዚህ መፍትሄ ነው ብሎ የሚያስበው “ይህን ቅስቀሳ የሚያካሄዱ ወገኖችን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ“ ማጥፋትን ነው። አለበለዚያ “ይህ ሕዝብ ከነቃብን አይመለስልንም“ ብሎ ያስባል እንጂ የሕዝቡን ገደዶች (concerns) እና ጥያቄዎች ማስተናገዱን እንደዋነኛ መፍትሄ አይወስደውም (ገጽ 136) ።
በዚህ ረገድ ዳኛቸው ለደርግ ያለው ታማኝነት የሚገለጸው በአብዛኛው ሥርዓቱን በየትኛውም መንገድ ሥልጣኑን እንዲቆናጠጥ ከማድረግ አንጻር እንጂ፣ ሕዝባዊ መሠረት ይኖረው ዘንድ ከመትጋት አይደለም። በመሆኑም የመለዮ ለባሹንም ሆነ የተማሪውን፥ እንዲሁም በጠቅላላው የህዝቡን ጥያቄዎች በማስታወሻው ይከትባቸዋል፣ ነገር ግን በየትኛውም መድረክ አቅርቦ ሲያወያይባቸው አይታይም። ለመንግሥት ቅርብ የመሆኑን ያህል ለሕዝቡ ባይታወር ይመስላል።
ደርግ የቆመለት ዓላማ ሥልጣን ብቻ ነበር እስከምንል ድረስ ዳኛቸው የሚሳተፍባቸው አሰልቺ ስብሰባዎችና ሁነቶች ሁሉም ማለት ይቻላል ሥልጣንን ከአደጋ የመጠበቅ ትግልን መሠረት ያደረጉ ናቸው። በመሃል ሕዝብ በሥርዓቱ የአትኩሮት ክበብ (focal area) ውስጥ የት ጥግ እንዳለ ለማየት ግራ እስኪገባን ማኅበራዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ባሕላዊ ጭብጦች በወጉ አይነሱም። በደርጉ ውስጥ የተፈጠሩ የተለያዩ ቡድኖች ሴራ (conspiracy) እና የኋላ ኋላ ዳኛቸው ራሱ ሰለባ የሚሆንበት አንዱ ሌላውን ጥሎ የማለፍ ትግል የፈጠራቸው የሥጋት፥ የክፋት፥ የጭካኔና የተንኮል እንቅስቃሴዎች አስኳል ነው - ዳኛቸው። ለዚህም ይመስላል ተራኪው “ደርግ ማለት ዳኛቸው፥ ዳኛቸው ማለት ደርግ ነውና ለቆመለት ዓላማ ይሞታል፥ ይዋደቃል“ በማለት የገጸ ባህሪውን የዘመን ተምሳሌትነት የፈነተወው (ገጽ 36) ።
ያም ሆኖ ዳኛቸው ወረደ ለለውጥ ፍጹም ባይታወር የሆነ ገጸ ባህሪ አይደለም። ለማወቅ ጉጉ ከመሆኑ አንጻር በሂደት እየተማረና እየተራመደ የመሄድ አዝማሚያ የሚያሳይ ሰው ነው። ሲጀምር አንዳንዴ የማመዛዘን ችሎታው ለነበረበት ደረጃና ለሚጠበቅበት ኃላፊነት የሚመጥን አይመስልም ነበር። ለምሳሌ በደርጉ ላይ ከተነሱ “አድሃሪዎች“ እጅ የወጣ በምስጢር የተሞላ ደብዳቤ ካነበበ በኋላ በኮድ ስም የተጠቀሱ የደርግ አባላትን ከእውነተኛው የደርግ አባላት ስም ዝርዝር ውስጥ ለማግኘት ሲሞክር እንታዘበዋለን። መፈለግ ብቻ አይደለም የተጠቀሱትን ስሞች ከዝርዝሩ ሲያጣ፣ “ምናባታቸው ነው የሚቃዡት! እንዲህ እንዲህ የሚባሉ የደርግ አባላት የሉም“ (ገጽ 56) ብሎ ይደመድማል እንጂ ስሞቹ የምስጢር ስሞች ሊሆኑ እንደሚችሉ ላፍታም አይታሰበውም። ይህ አሳሳል (characterization) “በእውኑ በዚያ የሕቡዕ ትግል በተስፋፋበት ዘመን አንድ ጎምቱ የደርግ ባለሥልጣን ይኸን ያህል ለትግሉ ባሕሪ እንግዳ ይሆናልን?“ የሚል የተአማኒነት ጥያቄን ሊያጭር ይችላል የሚል እምነት አለኝ። ያም ሆኖ ደራሲው የገጸ ባህሪው ግልብ ሰብእና መነሻ አድርጎ በመጠቀም አግባብነቱን ሲያጸድቀው ይታያል።
እዚህ ጋ ይህን ክፍል ስደመድም ለምገልጸው አንድ ጉዳይ ዋቢ እንዲሆነኝ የዳኛቸውን ሌላ ጉልህ ጠባይ ልጠቁም። ዳኛቸው የሴት ነገር አይሆንለትም። ለወሲብ ያለው ፍቅር ሌላውን ሁሉ ጉዳይ እስከማስረሳት የሚያደርስ ኃይል አለው። በዚያው ልክ ለሴቶች ያለው አክብሮት አበጀህ የሚባልለት አይደለም። ለምሳሌ አብልጦ እንደሚወዳት ከተገለጸልን ከስንዱ ጋር ትውውቅ ሲጀምር የነበረውን አጋጣሚ መጥቀስ እንችላለን። ስንዱ ያገር አስተዳደር ሚኒስትሩ ጸሃፊ ስትሆን ዳኛቸው የቅርብ ወዳጁ ወደሆነው ወደዚህ ሚኒስትር ቢሮ የሄደ ጊዜ ያያታል። ኮሎኔሉ ሚኒስትር ከዳኛቸው ጋር ሲያስተዋውቃት፣ ዳኛቸው፣
“እንተዋወቅ... ስምሽ ማነው?“ አለና ከእግር እስከራሷ እያስተዋላት ባይኖቹ ሰለቀጣት።
“ስንዱ...“ አለች።
“አለቃ ካመሰገነ ሠራተኛውን ይሰስታል እንድሚባለው ካልሆነ ጥሩ ነው“ አለ።
“በፍጹም በፍጹም!... ልትሾማት አሰብክ ወይስ...“ አለና ሊናገር የፈለገውን ገታ አድርጎ፣ አብሮት ሳቀ (ገጽ 34) ።
ይህን የሚባባሉት ስንዱ አጠገባቸው እያለች ነው። በመሃላቸው በመሆኗ እንኳ የሚገባትን ክብር አልሰጧትም።
ዳኛቸው “ላንተ ካልፈለካት እኔ ልወዳጃት“ ሲልና ኮሎኔሉም “ከፈለካት እነሆ...“ ብሎ ቀድሞውኑ እንዳቀደው ሲመርቅለት በመሃል ሴቷን ልጅ እንደፍትወት ጥማት ማርኪያ (sexual object) እንጂ በራሷ እጣ ላይ የመወሰን መብት ሊኖራት እንደሚገባ እኩል ሰብዓዊ ፍጡር አያይዋትም። (ለነገሩ ስንዱም ብትሆን ለራሷ ዓላማ የዳኛቸውን ወዳጅነት ትፈልገው ስለነበር ሴትነቷን ከጥቅም መሳሪያ ቀፎነት አሳልፋ የምታይ አልነበረችም። በራሷ መንገድ ቤተሰባዊ የሴራ ድሯን በማድራት የመጠላለፉን ሌላኛ ገጽታ የምትመራ ገጸ ባሕሪ ናት።)
ከስንዱም ሆነ ከሌሎቹ ሴቶች ጋር ዓላማው “እንደውኃ ጥም“ ሊረካቸው ከመፈለግ የዘለለ ሆኖ አንዳች የአፍቃሪ ቁምነገር ሲሠራ አይታም። ሴትን ልጅ እንደሸቀጥ የማየት ባህሪም ይታይበታል። ለምሳሌ የምድር ባቡር አገልግሎት እንደገና መጀመሩን የሚያበስር ዜና በቴሌቪዥን ሲመለከት፣ በምናቡ የሚጓጓዘው ሸቀጥና ኮተት በዓይነ ሕሊናው ሲታየው፣ “ጫቱ፥ ፍራፍሬው፥ ቡናው፥ እህሉ፥ በጉ፥ ፍየሉ፥ ሰንጋው፥ ሴቱና ሌላ ሌላውም“ እየታሰበው ነው (ገጽ 43) ። የሚገርመው ደግሞ ሐረርና ጅቡቲ ድረስ በምናቡ ዘልቆ ነገረ-ሴት የሚከሰትለት ስንዱ ለአዳሯ ወደእሱው ቤት እየመጣች በነበረችበትና እሱም በጉጉት እየጠበቃት በነበረበት ምሽት ነው።
“ጥሎ ማለፍ“ን ከታሪካዊ ይዘቱ በተጨማሪ እስከወዲያኛው በስሜት እንድናነበው ከሚያደርጉን ጉዳዮች አንዱ የዳኛቸው ሰብእና የለውጥ ሂደትና የሕይወት ገጠመኙ ይመስለኛል። ሲጀመር ከየትኛውም የደርግ አባል ለይተን የምናይበት ባህሪ አልነበረውም። ወዲያው ግን መልአከ ሞትን ከመጥራት ውጭ ሌላ መልክ ከማያሳዩ ጽንፈኛ የደርግ አባላት አንጻር ዳኛቸው የሚያሳየውን የተለሳለሰና ያስታራቂነት አቋሙን ስንመለከት ሙሉ በሙሉ አስተዋይነት የራቀው አለመሆኑን እንገነዘባለን። በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የሚያሳያቸው የተሻሉ ግንዛቤዎቹና አቋሞቹ በመጠላለፍ ታሪኩ የሚወጠርን ሕሊና ፋታ የመስጠትና ስሜትን የማለዘብ ሚና ያላቸው በመሆኑ፣ የኋላ ሕይወቱን ድቀት (tragedy) ከጭፍን ደርጋዊ ሰብእናው አንጻር ብቻ ሳይሆን፣ በሂደት ከተማራቸውና ከተገነዘባቸው ሕዝባዊና ፖለቲካዊ እውነታዎች አኳያም እንመለከተዋለን።
በተጨማሪም ዘመንና የሕይወት ተመክሮ ከማይለውጣቸው ድድር ወደረኞቹ አኳያ እየመዘንን እንድናዝንለት እንጂ „የዋጋውን አገኘ“ በሚል የበቀል አረዳድ (vindication) ፍርዳችንን እንድንሰጥ የደራሲው “መሐሪ“ ብዕር የፈቀደ አይመስልም። አልፎ አልፎ ያልጠበቅነውን ሰብዓዊነት በዳኛቸው ውስጥ እናያለን። ለምሳሌ ከጓድ መንግሥቱ ጋር ሆነው በአንድ የኢሕአፓ አመራር አባል ላይ ምርመራ ሲያካሄዱ ምርመራው ለሚካሂድበት “የጠላት ወገን“ ሀዘኔታ ያሳያል። የተመርማሪውንም የአቋም ጽናት በልቡ ያደንቃል። ይህ አድናቆቱ ራሱ ዳኛቸው ባረገዘችው ጓደኛውና በሱ የወደፊት ሕይወት ላይ እንኳ አቋም ለመውሰድ ከተቸገረበት ሁኔታ ጋር አብሮ መቅረቡም አንዳች ምጸታዊ ፋይዳ ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ዳኛቸው ወረደ የሚያልፍበት የለውጥ ሂደት የደርግን መስመር የሚያስከዳ ዓይነት አይደለም። ሆኖም በተለይ ከውጭ አገር ትምህርቱ በኋላ ሥርዓቱ የጥርጣሬ ዐይኑን ያሳርፍበታል። የትምህርቱን ፍሬ አይደለም የመጠሪያ ማዕረጉንም የሚቀበል ደንብ አይኖርም። በተወሰነ ደረጃ በግርማቸው ተክለ ሃዋርያት “አርአያ“ ታሪካዊ ልቦለድ ውስጥ ዋናው ገጸ ባህሪ አርአያ የገጠመውን ዓይነት የማያላውስ የሥራ አካባቢ (ግን ደሞ የባሰ) ሲገጥመው እናያለን። ነገር ግን ዳኛቸውም ቢሆን ባንዳች ተዓምር መሳይ ውሳኔ በሁለት ዓመት ጥናት የተመረቀለትን ዱክትርናና ከዚያውም ጋር ተያይዞ ሊያገኝ ይናፍቅ የነበረውን ሥልጣን አልፎ የእውቀቱንና የገጠመኙን ትሩፋት ለወሳኝ ማኅበረ-ፖለቲካዊ ለውጥ የማዋል ቀናኢነት አይታይበትም።
እንዲህ እንዲህ እያለ የሚዘልቀውና በውጣ ውረድ የተሞላው የዳኛቸው ወረደ ሕይወት ሰውዬው አጥብቆ ይወዳቸው የነበሩትን ሁለት ነገሮች በመጥላት ምጸት (irony) ይደመደማል - ደርግንና ሴትን ልጅ አምርሮ ይጠላል።
ደርግን እንዳምላኩ ያይ ያልነበረውን ያህል ለውዴታው እውቀታዊና እውናዊ መሠረት ያጣለታል። እንደዚያው የፍትወትን ጥማት ከማርካት ውጭ ፍቅር፥ ክብርና መናበብ (understanding) ያልነበረው የሴት ልጅ እይታው ከፖለቲካ ህይወቱ ትይዩ ሌላ ጥሎ የማለፍ ቤተሰባዊ ትብትብ ውስጥ አስገብቶት ያርፈዋል። በመከያው መውጫ መግቢያ ያጣች ነፍሱን እያነበብን የተሻልን ከሆንን የምናዝንለት፣ የሱ ብጤ ከሆንም የምንማርበት (ልቡ ካለን) ብኩን ገጸ-ሰብ ሆኖ ያልፋል - ዳኛቸው ወረደ።
ለ. ታሪክ (STORY)
በገጸ ባሕሪ ዳሰሳዬ ላይ በተወሰነ መልኩ ስላቀረብኩት ታሪኩ ላይ ብዙ ጊዜ አልወስድም። በርዕሱ ላይ እንደተመለከተው ሁሉ፣ ታሪኩ ጥሎ የማለፍ ታሪክ ነው። ሰርክ መጠላለፍ፥ መፈራራት፥ መገዳደል ወዘተ... የሞላበት፥ አንዱ የደርግ አባል ወይም ቡድን ለሌላው የማይተኛበት፥ ኃላፊ የበታች ሠራተኞቹን የማያምንበት (በተለይ በመንግሥት ሚዲያ አካባቢ ያለውን ሁኔታ በሚዘግበው ታሪክ በኩል እንደምንመለከተው) ወዘተ... አንዱ አንጃ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ሌላውን በልቶ ለመደንደን የሚታትርበት፥ የሚመሳጠርበትና የሚያሴርበት ታሪክ ነው። እንደኔ እይታ የልቦለዱ ታሪካዊ ይዘት በግሩም መንገድ ከመሰነዱ ባለፈ፣ በጊዜው ኖረን ላየነውም ሆነ በንባብ ለምናውቀው ለዚያን ዘመን መልክ ቅርብ ነው። የተለየ ይዘት የለውም፣ እንዲኖረውም አይጠበቅበትም - ታሪክ ነውና።
የታሪኩ ይዘት በወቅቱ በተጻራሪነት የቆሙ የፖለቲካ ኃይሎችን አቋም ያስተዋውቃል። እነዚህን ቡድኖች በጥቅሉ በሦስት ቡድኖች ከፍሎ ዓላማቸውን ይገልጻል። በዚሁ መሠረት አንደኛው ወገን “ሕዝቡ የሥልጣን ባለቤት መሆን አለበት... ደርግ የሠራተኛውን መደብ ከሥልጣን ባለቤትነት ፈንቅሏል“ ብሎ ያምን ነበር። ሁለተኛው ወገን በበኩሉ ሠራተኛው ስላልነቃ፣ ስላልበቃና ስላልተደራጀ ሥልጣኑን ለመያዝ አይችልም ብሎ የሚያምን ስለነበር ከደርግ ጋር የታክቲክ ግንኙነት ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ነው። ሦስተኛው ደርግን እንደሠራተኛው መደብ የሚቀበልና ከሥርዓቱ ጋር የመርህ ትብብር ያደረገ ያም ሆኖ የማይተማመንና አንዱ ሌላውን ጥሎ ለመውጣት የሚሠራ ነው (ገጽ 36/37) ።
ከዚህ የትግል መስመር ልዩነትና የሥልጣን ፍቅር የሚመነጨው የመጠላለፍ ታሪክ ያንባቢን ሕሊና ሰቅዞ የመያዝ ጉልበት አለው። በተለይም በራሱ በደርጉ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ቡድኖች መካከል ያለው ፍትጊያ ፋታ በሚነሳ ሁኔታ የቀረበ በመሆኑ አእምሮን አስጨንቆ የትዝብት እይታን የሚያሰላ ነው።
እንደታሪክነቱ በእውን የሆኑና የተከሰቱ ጉዳዮችን ይዘግባል። የወዛደር ሊግ በአብዮታዊ ሰደድ ውስጥ ሰርጎ ገብቶ ኢማሌድህን ለብቻው ለመቆጣጠር ሲሠራ ደርሰንበታል፣ ዶ/ር ሠናይ ልኬ አብዮታዊ ሰደድን የወዛደር ሊግ ወታደራዊ ክንፍ ለማድረግ ሠርቷል፣ ተከታዮቹም የሱኑ ዓላማ ሲያራምዱ ተገኝተዋል፥ ወዘተ... የሚሉት እነጓድ ሊቀመንበር የቅጣት ሠይፋቸውን ይመዛሉ። የወዝ ሊግ አባላት በየስብሰባው ይብጠለጠላሉ፥ይዋከባሉ፥ ይታሠራሉ፥ ይገደላሉ። ከነሱም አልፎ ለደርጉ ያላቸው ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የማይገባው የዳኛቸው ወረደ ዓይነቶቹ ጭምር በልጠው እንዳይታዩ ይኮረኮማሉ፥ መቀጣጫም ይሆናሉ። ሾኬ መመታታቱ፥ እስሩና ግድያው የዘመኑ የየእለት ገጠመኝ እንደመሆኑ ፖለቲካው ፍርሃት፥ ሥጋት፥ ጥርጣሬና ክህደት የበዛበት ነው። አቀራረቡም ይህ ጽልመታዊ ድባብ አንባቢን እንዲጫነው የሚያደርግ ነው።
እንደልቦለድነቱ (ታሪካዊ መሆኑ ሳይረሳ) ደግሞ ደራሲው በግሩም የምናብ አድማሱ የታላላቆቹን ተዋንያን የርስበርስ ግንኙነት፥ የስሜት ተራክቦና ልውውጥ በሚጥም ቋንቋና ድራማዊ አቀራረብ ከስቷቸዋል። እንደታሪኩ ባለቤቶች ደግሞ በርትቶ ለማመሳከር ጥረት ላደርገ ልቦለዳዊ ስሞቹን ከእውናዊ ማንነታቸው ጋር አገናኝቶ ያውቃቸዋል። በጥሬው የታሪክ ይዘት ዘገባው ብቻ እንዳንሰላች (የልቦለድ ባህሪም ነውና) በፈጠራቸው እውነት አከል አውዶችና ትእይንቶች አማካይነት የዘመኑን መንፈስ በልቦለዱ ሁለንተናና በታሪኩ ወርድና ቁመት (framework) ልክ አሳምሮ ቀምብቦታል ወይም ሰፍቶታል ማለት የሚቻል ይመስለኛል። የዚያኑ ያህል ባለንበት ዘመን ያለው ያገራችን ፖለቲካ ከዚህ የጥሎ ማለፍ አባዜ የተላቀቀ እንዳልሆነ የምንገነዘብባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። ከዚያ በተረፈ በግሌ ከዚህ በፊት “ነበር“ በሚል ርእስ የደርጉን የውስጥ ጣጣ በዘገበ መጽሃፍ ውስጥ ጓድ መንግሥቱ የቀረቡበት መንገድ ቀደም ሲል ስለሰውዬው የነበረኝን የርቀት ግንዛቤ ጥያቄ ውስጥ አስገብቶት ነበር። “ጥሎ ማለፍ“ ታሪካዊ ልቦለድም እንዲሁ ከብሄራዊ ስሜታቸውና ጭካኔያቸው ባሻገር የሰውዬውን ፖለቲካዊ ብልጣብልጥነት በድጋሚ እንድረዳው ያደረገ መጽሃፍ ነው። በተለይም በዙሪያቸው የከበቧቸውን ሰዎች የርስ በርስ ግንኙነት ጥርጣሬ የተሞላበት በማድረግ ወደራሳቸው የተቃጣን የትኩረት አቅጣጫ አስቀይረው ራሳቸውን ነጻ የማውጣትና ሥልጣናቸውን የመጠበቁን ብልሃት የተካኑ እንደነበሩ ለመታዘብ አስችሎኛል።
ዳኛቸው ወረደ ዘብጥያ ከወረደበት ከደርጉ ጽ/ቤት ትንሽ ክፍል ውስጥ ሆኖ የንባብ አድማሱን እያሰፋ በሄደበትና ከራሱ ጋር መነጋገር በጀመረበት ሂደት ውስጥ የደርግ የፖለቲካ አካሄድን መለስ ብሎ በተረጋጋ መንፈስ ለማየት ይሞክራል። ሁኔታው ለዳኛቸው የደርጉን ዓለም በእውቀት ላይ ተመስርቶ የሚያይበት እንደመሆኑ የአፍላጦንን (Plato) የዋሻ ትምህርት (parable of the cave) ተምሳሌት ያስታውሰኛል። በዚሁ ሁኔታው ውስጥ ሆኖ በሚያደርገው ሕሊናዊ ጉዞ ራሱንና ሥርአቱን መለስ ብሎ የማየት እድል ያገኛል። በሱ ያስተሳሰብ ለውጥ በኩል የደርግ መሠረታዊ ችግሮችና ሕጸጾችም የታሪኩን ይዘት ያጎለምሳሉ። ከዚህ ዋሻ በሚነጠቅልን ትምህርትም ደርግ ስልጣንን ለማጽናት በራሱ ላይ ሳይቀር ተደጋጋሚ ኩዴታ እያካሄደ የሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ጎራ የወሰዳቸው ግብታዊ ርምጃዎች፥ ድብቅ አካሄዶችና ያስከተሏቸው ጥፋቶች ይተነተናሉ። ዘመኑን ተመልሶ ለማየትና ለመማር የፈለጉ ሁሉ ብዙ ቁምነገሮችን ያገኙበታል - ከታሪካዊ ልቦለዱ።
ሐ. ቋንቋ
ስለቋንቋው ብዙ ማለት የሚቻለው ጥልቅ ምርምር ማድረግ ሲቻል በመሆኑና በዚህ ረገድ በቂ ጊዜ አግኝቼ ለማጥናት ስላልቻልኩ ጠቅለል ያለ እይታዬን ነው የማቀርበው። “ጥሎ ማለፍ“ የቀረበበት ቋንቋ ቀላልና ታሪኩን በፍጥነት ይዞ የመጓዝ ብቃትን የተላበሰ ነው። ለዚህ ፈጣን የታሪክ ጉዞ ጉልህ አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች ውስጥ ደራሲው ታሪኩን ለማቅረብ የመረጣቸው አጫጭር አረፍተ ነገሮች ዋነኞቹ ይመስሉኛል። በአንድ ቃል ሳይቀር የተሠሩ ተደጋጋሚ አረፍተ ነገሮችን እናገኛለን። ለአብነት ያህል አንድ ሁለት አንቀጾችን እንመልከት....
ኢትዮጵያ ተወጥራለች። በውስጥ በውጭ እንደላስቲክ እየተሳበች ትለቀቃለች። በየከተማው በየገጠሩ ተስቦ የተለቀቀው ውጥረት ያገኘውን ይጠብሳል። ያገኘውን ያሳርራል። ከደጅ ደጅ፥ ከቤት ቤት፥ ከቢሮ ቢሮ፥ ከከተማ ከተማ... እያንዳንዱን ሰው ያነፈንፋል። ሽብር፥ ፍርሃት፥ሞት የሁሉም የቅርብ አስታዋሽ ሆኗል። በዚህ ሁሉ ትርምስ ውስጥ ሥልጣኑን የያዘው የጊዜያዊው ወታደራዊ መንግስት ይንጠራሞታል። በብዙ ጥበብ ከእጅ የገባው ሥልጣን፥ እንዳያፈተልክ ቆቅ ሆኖ ይጠብቃል። በሥልጣኑ የመጣ ባይኑ ብቻ የመጣ አልነበረም፣ መተኪያ በሌላት በእያንዳንዱ የደርግ አባል የግል ሕይወቱ ጭምር እንጂ... (ገጽ 22)
ይህ አንቀጽ በበርካታ አጫጭር አረፍተ ነገሮች ዝርዘራ የተሞላ አጭር አንቀጽ ነው - ግን ብዙ ነገር ማለት የቻለ። የአገሪቱን መልክ ይገልጻል፣ ሕዝቡ ያለበትን አስጨናቂ ሁኔታም እንዲሁ... በዚያው ልክ ደርግ የሚገኝበትን ፈታኝ ጊዜና አቋሙን ጥርት አድርጎ የሚያሳይ ነው። በአጫጭር አረፍተ ነገሮች ብዙ ነገር ማለትና ታሪኩን በፍጥነት ማራመድ የአበራ ለማ የተመረጠ ዘዬ (style) ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ሌላ አንድ ምሳሌ ላክል...
ወዲያው ደሞ አንድ ሌላ ሃሳብ መጣበት። ‘ምናለ ባገባትስ? ብትወልድስ?... ስንዱ ውብ ልጅ ነች። ቆንጆ ነች። ባል ከፈለገች አማርጣ ማግባት የምትችል ነች። ያረገዘችልኝ ብትወደኝ እንጂ ለሌላ አይመስለኝም...‘ እያለ መልሶ ለራሱ ይፈግጋል። እራሱን በእድለኛነቱ ያግባባል፥ ያጽናናል። ወዲያው ደሞ በሌላ ሃሳብ ይጠለፋል። ‘ግንኮ ስለማንነቷ ምንም የማውቀው ነገር የለኝም። እንዳጠናት እድል አልሰጠችኝም። በጣም ፈጠነችብኝ። ካረገዘች መጋባታችን ነው... ከተጋባን በትዳር ዓለም ልንዘልቅ ነው። ግን ግን ምን ያህል ተዋውቀናል? የነቶሎ ቶሎ ቤት... ዓይነት ቢሆንስ?...‘ እያለ በሃሳብ ጢሎሽ ውስጥ ሽቅብ ቁልቁል ተናጠ (ገጽ 150) ።
ይህ እንግዲህ አንድ በሃሳብ “ሽቅብ ቁልቁል“ የሚናጥ ሰው ወደ ውስጡ የሚያደርገውን ሃሳባዊ የጉዞ ውጣ ውረድ (dilemma) ለመከሰት ደራሲው በብቃት የተጠቀመበት በአንድ ቃል ሳይቀር የተሠሩ አጫጭር አረፍተ ነገሮች ሰንሰለት ነው። የሃሳብ ሰንሰለቱ ገጸ ባህሪው የሚገኝበትን ሕሊናዊ መጨናነቅ አንባቢውም እንዲሰማው የማድረግ ኃይል ያለው ነው።
ከዚህ በተረፈ ቋንቋው በዘይቤም ያሸበረቀ ነው። ጥቂት ምሳሌዎችን ብቻ ልጥቀስ። የጓድ መንግሥቱን የማእርግ ልብስ አለባበስ እንደሚከተለው ይገልጸዋል።
የእለቱ አለባበሳቸው ሙሉ ቅጠልያ ወታደራዊ ዩኒፎርም ካኪ ነው። የሌተናል ኮሎኔል ማዕርጋቸው ኮከብ ከወርቅ እንጂ ከሌላ የብረት ዘር የተሠራ አይመስልም - ሲያብረቀርቅ። ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ያንን ልብ የሚል የለም። ባይሆን ከቀዩ የማርሻልነት ማዕርግ ምልክታቸው ላይ እንጂ፥ ዓይኖቻቸው የሚያርፉት። (ገጽ 82)
እንደወርቅ የሚንቆጠቆጠውን የማዕረግ ምልክት አፍዝዞ ቀዩን የማርሻልነት ማዕረግ ያጎላው ያለፋይዳ አይመስለኝም። የደም ሃብታም የሆነውን የሰውዬውን አመራርና ሥርዓት እንዲሁም ሁኔታው የሚፈጥረውን የፍርሃትና የሽብር መንፈስ ለማንጸባረቅ እንጂ።
ደራሲው ማለፊያ የውበት አገላለጽ ችሎታም አለው። ውበትን መግለጽ ብቻ አይደለም፣ ውበቱ በተመልካች ዘንድ የሚፈጥረውን ስሜትም በጥሩ መንገድ ይገልጸዋል። ለምሳሌ የሚከተለውን እንመልከት...
ዳኛቸው ላንዳፍታ ስንዱን በውስጡ አገላብጦ አሻሻት። ጠይም ነች። ቁመትዋ መለስ ብሎ፥ ቀጥ ያለ አቋም ያላት። የሰውነቷ ውፍረት መካከለኛና ስትራመድ የዓይን ወለምታን የምትጋብዝ... ዞማ ጸጉሯ ባጭሩ ተቆርጦ፣ ከወደ ግምባሯ መለስ በማለቱ፣ ጥርት ካሉት የጎሉ ዐይኖቿ ጋር ሲስተዋል መስተፋቅርን የሚሠራ... በዚህም እኔ ነኝ የሚል የወንድ ኮስታራን ቀልብ የምትገፍ። ከፊቷ ላይ ፈገግታ እንዳይለያት ሲሉ ጥርሶቿ እንደታማኝ ሞግዚቶች የሚያገለግሏት የሃያ አምስት ዓመት ወጣት ነች። ከሱሪ ይልቅ ቀሚስን ስለምታዘወትር የባቷ የተስተካከለ ቅርጽ ሌላው ውበቷን የሚያጎላላት መስህቧ ነው ( ገጽ 32/3)።
ገለጻው የልጅቷን ውበት ቁልጭ አድርጎ ከማሣየት አልፎ በተመልካቹ ላይ የሚፈጥረውን የመጎምዠት ስሜት ይከስተው ዘንድ ሲጀምር ዳኛቸውን፣ “...በውስጡ አገላብጦ አሻሻት“ ብሎ ሃሳባዊ የፍትወት ተግባር ውስጥ ይከተዋል። እንዲያም ሲል ያን ውበት እያየን የሚፈጠርብንን የመደናገጥ ስሜት፣ “...ስትራመድ የዓይን ወለምታን የምትጋብዝ...“ በሚል ስሜት ብቻ ሳይሆን ድርጊት ከሳች በሆነ ውብ ቋንቋ ያሳየናል። ወዲያውም የወለምታን ስሜትና ቃሉን እራሱን በልማድ ከቆረበባቸው ምላስና ጉልበት አፋትቶ ለአፍታም ቢሆን ከዐይን ጋር ያጋባዋል። ሁላችንም ያይን ወለምታ ምን እንደሚመስል ለመረዳት በየራሳችን ላይ ሙከራ እንድናደርግ ያስጋብዛል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የወሲብ ስሜት ትዕይንት አቀራረቡ ማራኪነት በአብዛኛው ተግባሩ ከሚገለጽበት ቋንቋና ተዋንያኑ ካሉበት የስሜት ግላጼ (expression) እንጂ አሁን አሁን ባገራችን በሚጻፉ መጻህፍትና ሌሎች የጥበብ ውጤቶች ውስጥ እንደምንታዘበው ወሲብን በደረቁ አግጥጦ ከማቅረብ ተግባር የሚመነጭ አይደለም። ከዚህ አንጻር ደራሲው በደራሲነት እየታወቀ ለመጣበት የሥነ ስሁፍ ዘመን ታማኝነቱን ያሳየ ይመስለኛል። ለምሳሌ ስንዱ ዳኛቸው ዘንድ ላዳሯ በመጣችበት አንድ ምሽት ወደ ትዕይንቱ ከመግባቷ በፊት በምታደርገው የተረጋጋ ጉዞ (መታጠቢያ ቤት ውስጥ መቆየት፥ ልብሶቿን ተረጋግታ ማውለቅ ወዘተ...) እና በዳኛቸው ስግብግብነትና ትዕግሥት ማጣት (መቁነጥነጥ፥ ኋላም በስንዱ እርጋታ መሃል ድንገት የውስጥ ልብሷን “መዥርጦ“ ማውለቅ፣ ወዘተ...) መካከል ሆነን በጥሩ ቋንቋ ተከሽኖ የቀረበውን ድሪያና ወሲብ ሳይቆረቁረን እንድንታደመው ያደርጋል። የዳኛቸው ስግብግብነትና ጥማት “የናፍቆቱን፥ ያምሮቱን፥ የጉጉቱን ያህል አፈራረቃት“ በሚል አጭርና ፈጣን አረፍተ ነገር ሲገለጽ፣ ባንጻሩ የስንዱ መረጋጋት “ስንዱም በተራዋ ተረታች“ በሚል ሂደታዊና በስሜት የመሸነፍን ቅደም ተከተላዊ አመጣጥ በሚያሳይ ቋንቋ የቀረበ፣ የሁለቱን ስሜታዊ ልዩነትና አንድነት የሚያመለክት ነው።
በዚህ ክፍል መግቢያ ላይ እንደገለጽኩት፣ ስለቋንቋው ብዙ ማለት ቢቻልም፣ የበለጠ ምርምር የሚጠይቅ በመሆኑና እኔ ይህንን ማድረግ ስላልቻልኩ እዚሁ ላይ ይብቃኝ።
መ. ቀርነቶች
ማንኛውም የሥነ ጽሁፍ ሥራ (ልቦለድ፥ ኢልቦለድ፥ ወይም ጥናታዊ ጽሁፍ) ጉድለቶች ይኖሩታል። ሌላው ቢቀር ለጸሃፊው በአንድ ምክንያት ትክክል የመሰለው ነገር ለአንባቢው በሌላ ምክንያት ተቃራኒ ግንዛቤን ሊፈጥር ይችላል። እንከን የመሰሉኝን የሚከተሉትን ጥቂት ነጥቦች ሳቀርብ፣ በርግጥ እንከን ለመሆናቸው ተጠቃሽ የማደርገው ሌላ ሳይሆን የመጽሃፉን ሰናይ ገጽታዎች ለመቃኘት የተጠቀምኩበትን የራሴኑ ውስን ግንዛቤ (intellect) ብቻ ነው።
የመጀመሪያው ነጥቤ የሊቀመንበር መንግሥቱ መልክ የተገለጸበት ወጥነት የጎደለው ቋንቋ ነው። በተለይም የፊታቸውን ገጽታ ወይም ቀለም ደራሲው አንድ ጊዜ “ጠይም“ (ገጽ 90)፥ ሌላ ጊዜ “እንደወትሮው ሁሉ በጨው የታሸ መዳፍ መስሏል“ (ገጽ 72) ሲል ይገልጻቸዋል። በርግጥ መልካቸው የስሜታቸውን ጥላ እየተከተለ የሚቀያየር ነው ብሎ መከራከር ይቻል ይሆናል። ሆኖም በተለይ ጠይምነታቸው በተገለጠበት አረፍተ ነገር ላይ “ጠይም ፊታቸው በንዴት ጉበት እንደመሰለ ነው“ ስለሚል ሌላው መልክ ከንዲህ ዓይነት ስሜት ጋር ተያይዞ መምጣታቱን የሚያሳይ ነገር ባለመኖሩ፣ የመልክ መለዋወጡ ምክንያት ግልጽ ሆኖ የቀረበ አይመስለኝም። ጠይምነትን እንደወትሮ መልካቸው አድርጎ የተገለጸበት ቋንቋም “እንደወትሮው ሁሉ በጨው የታሸ መዳፍ መስሏል“ ከሚለው ሌላ ገለጻ ጋር የማይጣጣም ይመስላል።
አለባበሳቸውን አስመልክቶም አንድ ቦታ ላይ የለበሱት ሙሉ ቀይ ሰማያዊ ልብስ እና ቀይ ከረባት ተጠቅሶ ሰውየው “አንድ ከወደ ምዕራብ አፍሪካ ብቅ ያለ ዲፕሎማት መስለዋል“ በሚል አነፃፃሪ ዘይቤ ተገልጸዋል(ገጽ 98) ። አለባበሱ ከሌሎች አፍሪካውያን ዲፕሎማቶች በተለየ ሁኔታ በምዕራብ አፍሪካዊያኑ አቻዎቻቸው የሚዘወተር አይነት ለመሆኑ ርግጠኛ አይደለሁም።
በደርጉ ውስጥ ባሉ ቡድኖች መካከል የሚደረጉት ስብሰባዎች ውጥረቱን ሳይቋረጥ እንድንከታተለው በተከታታይ ምዕራፎችና ንኡስ ምዕራፎች መቅረቡ በጠቅላላ ጥሩ አቀራረብ ሊባል የሚችል ቢሆንም፣ የተወሰነ ፋታ በመሃል ቢኖር የአንባቢ ትእግሥት እንዳይፈተን ይረዳ ነበር የሚል አስተያየትም አለኝ።
በተጨማሪ አልፎ አልፎ የሚታዩ የተአማኒነት ችግሮች አሉ እላለሁ። ለምሳሌ ዳኛቸው ለቀናት ታስሮ በነበረበት ጊዜ ሚስቱ ስንዱ ቢሮ (መ/ቤት) ውስጥ ሲያንሾካሹኩ ትሰማለች ተብለው ከተገለጹት ወሬዎች በተጨማሪ ሰዎች በቀጥታ ለሷው እንደነገሯት ተደርጎ የሚቀርብልን ነገር፣ በግሌ“በውኑ ለሚስት እስር ላይ ስላለ ባሏ እንዲህ ተብሎ የነገራታል?“ የሚል ጥያቄ የሚያስነሱ ሆነው አግኝቼያቸዋለሁ። በተለይም የሚከተሉትን ልብ ይሏል...
“ወይዘሮ ስንዱ፥ እጅግ የሚዘግንን ወሬ ነው የሚሰማው። ጓድ ዳኛቸው መንግሥት ለመገልበጥ ሲያሴር ተገኝቶ ተያዘ ይላሉ... አቤት ! አቤት!...“ አንድ ሸምገል ያሉ የዘበኞች አለቃ ነበሩ (ገጽ 191)።
“ስንድዬ እኔ አፈር ልብላልሽ... ጓድ ዳኛቸው እምን ደረሰ? ጸረ አብዮተኛ ነው ተብሎ እንዲረሸን በጉባኤ ተወሰነበት ይባላል...“ አንዲት ነባር፥ የመዝግብ ቤት ሠራተኛ ነበረች (ገጽ 191)።
ሌሎች ጥቃቅን ነገሮችን አንስቼ ላብቃ። መንግሥቱ ለማ አሉት ተብሎ የቀረበው ቀልድ አዘል ቁምነገር (ገጽ 166) መቅረቡ አስፈላጊ ቢሆን እንኳ ሁኔታው ዳኛቸው የምሩን ስለቅስቀሳ አስፈላጊነት ለአንድ ታላቅ ጉባኤ ሪፖርት በሚያቀርበብት ሁኔታ ውስጥ (በጊዜው በቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ አስፈላጊነት ላይ ጠንካራ አቋም ነበረው) ትዝ ብሎት ፈገግ ይላል ለማለት የሚያስቸግር ይመስለኛል። ቀልዱ ሌላ ቦታ ቢፈልግለት ኖሮ አሰኝቶኛል። የአንዳንድ ቃላት አግባብነትም ግር ይላል። ለምሳሌ “እራሱን ከራሱ እኔነት“ የሚለው ድግግሞሽ (redundancy) “ከማንነቱ“ ከሚለው ግልጽ ቃል በምን ተለይቶ ወይም ተሽሎ ጥቅም ላይ እንደዋለ ለመረዳት አልቻልኩም። በተረፈ አልፎ አልፎ የፊደል ግድፈቶች፥ በተለይ ደግሞ በድንገት ያለምክንያት የሚለወጡ የፊደል ፎንቶች እንዲሁም ደስታ የተባለው ገጸ ባህሪ ደሳለኝ ተብሎ በስህተት የተጠቀሰበት ገጽ በሁለተኛው እትም እንዲስተካከሉ ቢደረግ መልካም ነው።
መውጫ
“ጥሎ ማለፍ“ ታሪካዊ ልቦለድን በጣም በግርድፉ ከሦስት የሥነ ጽሁፍ አላባውያን፥ ማለትም ከገጸ ባህሪ አሳሳሉ፥ ከታሪኩና ከቋንቋው አንጻር ለመቃኘት ሞክሬያለሁ። የቅኝቴ ይዘት በጥቅሉ ሲታይ የመጽሃፉን ታሪካዊና ሥነ ጽሁፋዊ ፋይዳ የሚያሳይ ቢሆንም፣ ከውይይት የመነሻ ሃሳብነት የዘለለ ጥልቀትና ሙያዊ አስተዋጽአኦ ይኖረዋል ብዬ አልሟገትም። ፈርጀ ብዙ ምልከታ ሊደረግበት የሚችለውን ይህን መጽሃፍ ኃያሲያን አንበብው ብዙ ሊሉን እንደሚችሉ ግን አምናለሁ። የዘመናችን ፖለቲከኞችም በ“ጥሎ ማለፍ“ በኩል ታሪክን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ያገኙበትና ከታሪክ ምጸት ይማሩበት ዘንድ እመኛለሁ።
zewgeart@yahoo.com
No comments:
Post a Comment