የዘመን ለውጥ ፍቺ ኖሮት ፈረንጅ ሲያከብረው በድምቀት
አፍሪካም ያግዘው ይዙዋል ለጥፋቱ እውነት ሲዶለት
ዘመነኛው ምእራባዊ ካባቶቹ ባየለ ርግጫ
እኛን ከኛ ጋር ሲያንጫጫ
በማያበራልን ብርሃን
በሚያሳፍረን ድርሳን
ባሸበረን ወፍራም ልሳን
እናውጃለን 'ሃፒ ኒው ይር'
አዲስ ጥፋት አዲስ አመት
በአውሮጳዊው የእብደት እለት
ሲጀመር አዲስ እቅድ
ሹል ትንፋሹ ሲያርበደብድ
ባውዛ አይደፍረው ጨለማችን ባለንበት ሲያስረግጠን
ያለነፍጥ እጅ ሲያሰጠን
አየሩ በደባ ሲጠን
ጸሃይ በምስራቅ እንዳትወጣ ተፈጥሮዋን እንድትገታ
በምእራብም እንዳትገባ ይልቁንም ልምዷን ትታ
እንድትዘልቅ ደምቃ በርታ
ጨረቃም ድርሽ እንዳትል በምስኪኖች የጠኔ አምባ
በአፍሪካዊ 'የጨዋ' ብሂል በምዕራባዊ ጭብጨባ
'አዲስ አመት እንኳን መጣሽ
ደግሞ እንዲሁ ባመት ያምጣሽ'
እያልን እናስቃለን
በእርጅናችን ምርቃት መዓት
ስልጣኔን ዕደጊ አልናት
በርቀት ሆና እያየችን
በርቀት ሆነን እያየናት፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment