Thursday, April 21, 2011

የአበራ ለማ 'ጥሎ ማለፍ' ታሪካዊ ልቦለድ አጭር ቅኝት


-በዘውገ አባተ (ኦ.ዩ.)
እንደመግቢያ
በ411 ገጾች (አባሪ ሳይጨምር) የቀረበው “ጥሎ ማለፍ“ ታሪካዊ ልቦለድ ከደርግ የ17 ዓመታት የአገዛዝ ዘመናት የመጀመሪያዎቹን ወሳኝ 14 ዓመታትና በአመዛኙ አዲስ አበባን መቼቱ በማድረግ መጠላለፍ የበዛበትን የዘመኑን የፖለቲካ ሕይወት የሚተርክ ነው። ደራሲው በመግቢያው እንደገለጸው ታሪካዊ ልቦለዱ “ካንድ የደርግ ቋሚ ኮሚቴ አባል ከነበረ ግለሰብ ሕይወት ዙሪያ የተጠነጠነ ነው።“ (ገጽ 6) ከዚህ አልፎ ግን የታሪካዊ ልቦለዱ ማዕከል የሆነው ዳኛቸው ወረደ የዘመኑን ፖለቲካዊ ገጽታና ድባብ፥ የባለሥልጣናቱን ሥነ ልቡናዊ፥ አእምሯዊና ፖለቲካዊ ማንነት ይናገርበት ዘንድ ደራሲው ከምናቡ አንቅቶ የተጠቀመው ገጸ ባሕሪ ይሁን አለያም አንድ በሕይወት የነበረን የደርግ አባል ሰብእና በመውሰድ ታሪኩን የጥበብ ሥጋ አልብሶ፥ የጥበብ እስትንፋስ ይዝራበት (እውነቱ ይኸኛው ይመስላል) ተብራርቶ የተነገረን ነገር የለም። ነገር ግን ከላይ በጠቀስኳቸው በሁለቱም መንገድ ይሁን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሙሉ በሙሉ የፈጠራ ውጤት በሆነ ገጸ ባህሪ በኩል ታሪካዊ ልቦለድን ማቀበል ይቻላል። ቁምነገሩ በሚነገረን ታሪክና ታሪኩ በሚወክለው ጊዜና ቦታ (መቼት) መካከል ባለው እውነተኛ ተዛምዶ ላይ ይመስለኛል።
መጽሃፉን እንዲያው በወፍ በረር ከሦስት የልቦለድ ዓላባውያን አኳያ ለመመልከት እሞክራለሁ። ‘‘ጥሎ ማለፍ‘‘ በቅርጽም ዳጎስ በይዘትም ሰፋ ብሎ የቀረበ ስራ እንደመሆኑ፣ መጽሃፉን በምልዓት ወይም በጥልቀት ለመቃኘት ጊዜውም አልነበረኝም። ድፍረቱንም አልሞክረውም። የመረጥኳቸው የመመልከቻ መነጽሮች የገጸ ባህሪ አሳሳል (ከዋናው ገጸ ባሕሪ አንጻር)፣ ታሪኩና ቋንቋው ናቸው። ከላይ በጠቀስኩት ቅደም ተከተል መሠረት እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ።